በሉሲ ወይንም ድንቅነሽ ቅሪተ አካል ላይ ላለፉት 8 ዓመታት የተደረገ ጥናት ከዛፍ ላይ ወድቃ መሞቷን አረጋገጠ፡፡ የአሁኑ ጥናት እስካሁን ላልተመለሱ ሁለት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ ነው ተብሏል፡፡ ጥናቱ ሉሲ ከትልቅ ዛፍ ላይ ወድቃ መሞቷና በአጭር ጊዜ በአካባቢው በነበረ ረግረጋማ ቦታ መቀበሯን እንዲሁም አልፎ አልፎ በዛፍ ላይ ወጥታ ትኖር እንደነበር ያረጋገጠ ነው፡፡ ምርምሩን ያደረጉት የአዲስ አበባ እና ቴክሳስ ሂውስተን ዩንቨርሲቲ ምሁራን ናቸው፡፡ የምርምር ቡድኑ መሪ ዶ/ር ሙሉጌታ ፍሰሃ እንደተናገሩት በተደረገው የሲቲ ስካን ምርመራ የድንቅነሽ አጥንት አሰባበር ከትልቅ ዛፍ ላይ ወድቃ መሞቷን አረጋግጧል፡፡ የአጥንቶቿ 40 በመቶ በአንድ ላይ መገኘት ሚስጥር ደግሞ ከዛፍ ላይ ስትወድቅ በፍጥነት በረግረግ መሬት ውስጥ መቀበሯ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ጥናቱ በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ ላለፉት 42 ዓመታት የነበሩትን ጥያቄዎች የመለሰ ነው ብለዋል፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ መንግስት የኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛነት የሚያጠናክሩ ምርምሮችን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚደግፍ ገልጸዋል፡፡ በተለይ በእነዚህ ጥልቅ ምርምሮች የኢትዮጵያዊያን ተመራማሪዎች ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሉሲ ወይንም ድንቅነሽ 3 ነጥብ 18 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያላትና ለሰው ዘር ምርምር መሠረት የጣለች ነች፡፡
Welcome to Yeshaneh Tube. Join our website and gate right information at the right time Yeshaneh Tube Path of wisdom