ክፉውን ያርቀውና ድንገት የመሬት መንቀጥቀጥ ቢከሰት ምን ያደርጋሉ?
ከአስፈሪ የተፈጥሮ ክስተቶች ውስጥ አንዱ ርዕደ መሬት ነው፡፡ በእርግጥ በመሬት ከመከዳት በላይ ምን ሊያስፈራ ይችላል፡፡
ዓለማችን በርዕደ መሬት መለኪያ የተለያየ መጠን ያላቸው የመሬት መንቀጥቀጦችን በየጊዜው ታስተናግዳለች፡፡
በእኛም ሀገር ባሳለፍነው ሳምንት እሑድ ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ አካባቢ፣ በዛሬው ዕለትም ከጠዋቱ 1 ሰዓት ከ37 ደቂቃ ገደማ በአዋሽ ፈንታሌ መካከለኛ የሚባል የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል፡፡
የተከሰቱት ርዕደ መሬቶች ንዝረታቸው እስከ አዲስ አበባ ድረስ መሰማቱ ለመሰል ክስተቶች እንግዳ የሆነውን ህዝብ ያስደነገጠውም ይመስላል፡፡
ምንም እንኳን በስምጥ ሸለቆ እና አካባቢው የመሬት መንቀጥቀጥ እና ንዝረት የተለመደ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ቢናገሩም ፤ ክፉውን ያርቀው እንጂ አደጋው ቢያጋጥም ምን ማድረግ ይኖርብናል የሚሉ ጥያቄዎች ከብዙዎች ተነስተዋል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጥ ባለንበት ሥፍራ ቢከሰት ድንጋጤን ውጦ እኚህን ነገሮች ለማድረግ መሞከር የራስንም ሆነ የወዳጅን ህይወት ለመታደግ ያግዛል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጥ ጊዜ የሚሰጥ አደጋ ባለመሆኑ እራስን ለማዳን ከቦታ ቦታ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ባሉበት ቦታ ከታች ያሉትን የአደጋ መከላከያ ነጥቦች ይተግብሩ፡፡
• የመሬት መንቀጥቀጡ እንደተሰማዎ አንገትዎን በሁለት እጅዎ አጥብቀው በመያዝ በጉልበትዎ ይንበርከኩ
• በቀላሉ የማይንቀሳቀሱ ጠንካራ ነገሮችን አጥብቀው ይያዙ
• እንደ ጠረጴዛ ያሉ ከላይ መከለያ ያላቸው ዕቃዎች ሥር መግባት በሚወድቅ ዕቃ ሊደርስ የሚችልን ጉዳት ይቀንሳል፡፡
- የሚይዙት ዕቃ እንዳይንቀሳቀስ ከጠንካራ ነገር ጋር በደምብ ያስጠጉት (ለምሳሌ ከቤት ምሰሶ ጋር)
• እንደ መስታውት ያሉ በቀላሉ ረግፈው ጉዳት ሊያስከትሉ ከሚችሉ ነገሮች ይራቁ
• ቤት ውስጥ ከሆኑ ሲሊንደር ጋዝ፣ የተለኮሰ ሻማ አሊያም ሌላ እሳት ሊፈጥር የሚችል ነገር ካለ ያጥፉ
• አሳንሰር ከመጠቀም ይቆጠቡ
• ወጪ ከሆኑ ኤሌክትሪክ የተሸከሙ ፖሎች፣ ዛፎች አሊያም ሌሎች የተተከሉ ነገሮች እንዳይወድቁብዎ መራቅ እና በተቻለ መጠን ሜዳማ በሆነ ግልጽ ቦታ ላይ መገኘት እራስን ከአደጋው ለመጠበቅ ያግዛሉ፡፡
Comments
Post a Comment