የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ18 ዓመት በፊት የተቋቋመውን የትግርኛ ቋንቋ እና ስነ ጹሁፍ ትምህርት ክፍልን፤ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ሊዘጋ ነው። በፍልስፍና ትምህርት ክፍል በመጀመሪያ ዲግሪ የሚሰጠው ትምህርትም፤ ከዚህ ዓመት ጀምሮ እንዲቋረጥ ዩኒቨርስቲው ውሳኔ አስተላልፏል።
አንጋፋው ዩኒቨርሲቲ ከእዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው፤ የትምህርት ክፍሎቹ ላለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት አዲስ ተማሪዎችን ባለመቀበላቸው ነው።
“ትግርኛ ለምን ተማሪ እንዳጣ ዋናው ምክንያት የታወቀ ነው። በጦርነቱ ምክንያት ነው። እሱ ጎድቶናል። ተማሪው በየት አድርጎ ይምጣ” ሲሉ የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ አቶ ሀድጉ ተካ የችግሩን ምክንያት አስረድተዋል። የትግርኛ ቋንቋ፣ ስነ ጹሁፍ እና ፎክሎር ትምህርት ክፍል አዲስ ተማሪዎችን ለመጨረሻ ጊዜ የተቀበለው በ2010 ዓ.ም ነበር።
እንደ ትግርኛ እና ቋንቋ ስነ ጽሁፍ ሁሉ በተመሳሳይ ምክንያት እንዲቋረጥ በዩኒቨርሲቲው ውሳኔ የተላለፈበት ሌላው የትምህርት አይነት፤ በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ የሚሰጠው የፍልስፍና ትምህርት ነው። የፍልስፍና ትምህርት ክፍል ከ2011 ዓ.ም ወዲህ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሀ ግብር አዲስ ተማሪዎችን አለመቀበሉን የትምህርት ክፍሉ ኃላፊው ዶ/ር ፋሲል መራዊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
Comments
Post a Comment